Thursday, February 21, 2013

የኢህአዴግ የመከላከያ ስራዊት - አስጨናቂ ድረስ (ከጉለሌ) Part 1


                      የኢህአዴግ የመከላከያ ስራዊት                                 የካቲት 12ቀን2005ዓ.ም.

ከ21ዓመታት የወያኔ አገዛዝና የመከላከያ ስራዊት ቀን እንዲከብር ከታወጀ ከ17ዓመታት በሁዋላ ለመጀመሪያ ግዜ ባሳለፍነው ሳምንት ለስባት ቀናት ተከብሯል፣ በባድመ አካባቢም የጦር ልምምድ መደረጉን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አሳይቷል፣በመዝጊያው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢህአዴግ ስራዊት ጠቅላይ አዛዥ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የኢህአዴግ  ስራዊት መከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፍርጌሳ፣ የኢህአዴግ ስራዊት ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በተገኙበት አንድ ለናቱ በሆነው በአዲስ አበባ ስታዲየም አክብረዋል፣ የሚገርመው ግን እውን እነዚህ ስዎች እንደመጠሪያቸው ባለስልጣኖች ሆነው ነው ንግግር ያደረጉት?፣ ሟቹ መለስ ዜናዊ የቤት አሽከር ይመስል ጠፍንጎ ይዞ በፈልገው አይነት ቀረፁዋቸዋል ያለሱ ጌታ፣ያለሱ አዋቂ፣ያለሱ ምሁር የለም ብለው ያምናሉ፣ ለዚህም ነው ከፈጣሪ በላይ እሱን ማምለክ የጀመሩትና ያለሃፍረት ባደባባይ የሚለፍፉት፣(ከጄኔራል ሳሞራ ይልቅ በዉትድርና ሙያም ሆነ በትምህርት የተሻሉ መኮንኖች አሉ)፣ በችሎታ ማነስ፣በራስ አለመተማመን፣የተስጣቸው ቦታ ከሚያስቡት በላይ መሆኑና፣በሌሎችም ምክንያት መመሪያ ጠብቀው ከመፈፀም ውጪ ሃሳብ እንኹዋን ማቅረብ አይችሉም ድፍረቱም ወኔውም የላቸውም። መለስ ዜናዊ ከሞተ በሁዋላ ሳሞራ  አጋጣሚዉን ተጠቅሞ ጄኔራል ሞላን ከአየር ሃይል ሊያነሳ ሞከረ የተፈጠረውን ቅፅበታዊ ሁኔታ ተመልክተናል፣ታጋይ ሳሞራ ምንም ማድረግ ካልቻለ ሌሎቹ ትላንት ከአናሳ ብሄረስብ በኮታ የተመደቡት ምን ማድረግ ይችላሉ? ችግሩ አሁን መመሪያ ስጪው የለም፣ግራ ተጋብተዋል፣ይህ በመከላከያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተከስተ ችግር ነው።
የኢህአዴግ ስራዊት ምን ይመስላል?
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስራቸዉን ባለፉት ስድስት ወራት እንዴት እንደተወጡት ፀሃይ የሞቀውና ብዙ የተባለለት በመሆኑ አልደግመውም፣ አሁን ደግሞ የኢህአዴግ ስራዊት ጠቅላይ አዛዥ ተብለዋል፣  ከስሞኑም የአፍሪካ የወቅቱ ፕሬዚደንት የሚል ሹመት ተቀብለዋል፣ የባለራዕዩ መሪያቸውን በሹመት ብዛት በለጡ፣ የነገውን መከራ አላስተዋሉም! ታምራት ላይኔን የረሱት ይመስላል አሁን ሁለቱም እምንትና ስልጣን ተቀያይርዋል፣በመሰርቱ እንኩዋንስ ሃይለማርያም ሳሞራም ስራዊቱን ማዘዝ አይችሉም።
አቶ ሲራጅ ፍርጌሳ የመከላከያ ሚኒስትር ከተባሉ ረጅም ዓመታትን አስቆጥረዋል፣ታዲያ በሃላፊነታቸው ምንም ጉዳይ መወስን አይችሉም፣ በጀት ከማዘጋጀት ውጪ፣ለስም ካልሆነ በቀር በመከላከያ ኖሩ አልኖሩ ምንም ለውጥ አያመጡም።
ጄኔራል ሳሞራ የኑስ የስራዊቱ ኤታ ማዦር ሹም የሚለው ማዕረግ ከሙሉ ጄኔራል ማዕረግ ጋር ተስጥቷቸው በቦታው ላይ ከተቀመጡ ከአስራ ሁለት ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፣ ምን ዓይነት የጦር ትምህርት አላቸው የአካደሚክስ  ዕውቀታቸውስ የት ነው ያለው? ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በተልኮ እንደሌሎቹ ሞክረው አልቻሉም፣ከሽፍትነት እንደመጡ በቀጥታ /ጄኔራል ቀጥሎ /ጄኔራል፣አሁን ደግሞ ዘለው ሙሉ ጄኔራል፣ሲስጣቸው በዝምታ ከመቀበል ውጪ ይከብደኛል/ያሳፍርኛል አላሉም፣ ማለትም አይችሉም፣ዝም ብሎ መቀበል ብቻ አለቃቸው የነበሩት ስይ አብርሃና ታጋይ ሃየሎም አርአያ ጄኔራል አልተባሉም፣ሃየሎም ከቀብር መለስ የአሟሟቱን ምስጢር ለመሽፋፈን ጄኔራል ተብሏል፣የአሟሟቱ ምስጢር ተደብቁአል፣ታዲያ መለስ ዜናዊ የሚስጣቸውን መመሪያ ከመፈፀም ውጪ በስልጣናቸው ምን ስሩ? ምንስ ሊስሩ ይችላሉ? የራሳቸውን የግል የጥበቃ አባላትን እንኩዋን መምረጥና መመደብ አይችሉም፣ ከፊታቸው እንደ አርአያ/ሞዴል የሚያዩት የተማረ የጦር መሪ የላቸውም፣ ራሳቸውን በወታደራዊ ወይም በቀለም ትምህርት አላበለፀጉም፣መለስ ዜናዊ የሚላቸዉን በሙሉ ትክክል ነው ብለዉ ያለማወላወል ከመፈፀም ውጪ አስተያየት የመስጠት/የመቃወም አቅሙ የላቸውም፣በራስ የመተማመን ብቃቱም ችሎታዉም ስለሌለ እሳቸውም ለስም የተቀመጡ ጉዳይ ፈጻሚ ናቸው፣ሆኖም ባለፈው ዓመት በጤና መታወክ ምክንያት መልቀቂያ አቅርበው እንደነበር ይታወቃል  ዉሳኔ ሳያገኙ ግን መለስ ዜናዊ ዓረፉ።
አራቱ ዋና የኢህአዴግ ድርጅቶች(ህወሃት፣ብአዴን፣ኦህዴድ፣ደህዴን)የራሳቸው ጦር ሲኖራቸው የብሄረስብ ተዋጽኦ በሚል ሽፋን ከሌሎች ክልሎች የስው ሃይል በዝቅተኛ ደረጃ ይጨምራሉ፣ ወደ ከፍተኛው እርከን ግን አይታስብም፣ሲጀመር የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ ነው፣  በእርግጥ የጄኔራሎች ማዕረግ በኮታ ይስጣል ተማረ አልተማረ፣የእነዚህ አራት ድርጅቶች ስራዊት አቓም ምን ይመስላል?ተጠሪነታቸውስ ለማን ነው? የዕዝ ቀጠናቸውስ? በተባበሩት መንግስታት ሚሲዮን ሲላኩ ተዋፅኦው እንዴት ነው? ሶማሊያ የሚላከውስ ተዋፆኦ ምን ይመስላል? ይህ ሁሉ ተደማምሮ ስራዊቱን ለያይቶታል፣    
ከብዙ ዓመታት ቆይታ በሁዋላ አሁን በከፍተኛ ወጪ ለሰባት ተከታታይ ቀናት የመከላከያ ቀን ማክበር ለምን አስፈለገ? ሻቢያ በወታደራዊም በኤኮኖሚም አቅሙ ከደከመ ዓመታት ተቆጠሩ፣ እንክዋንስ ወረራ መፈፀም ራሱንም መጠበቅ የማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል፣ ሻቢያ ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት በቀላሉ ተሸንፏል፣ ያ ጦርነት በዚያ ሁኔታ መጠናቀቁ መለስ ዜናዊም ሆነ ሌሎቹ ፈፅሞ አልጠበቁትም፣ በወቅቱ የያዙትን ይዘው መደራደር ሲቻል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን አስጨርስው ስራዊቱን ከኤርትራ መሬት ማስወጣት ስህተት ነበር፣የፈሪ ዱላ ሆነና ነገሩ ደካማዉንና የተኮላሸዉን ሻቢያን ግን አስራ ሁለት ዓመታት ሙሉ ኦነግን ጨምሮ እንዳወገዘ የሃስት ድራማ በመስራት/በመወንጀል መቃብር ቀድሞ ወረደ፣ ለምንድነው ባድመ ላይ ሻቢያ ችግር እንዲፈጥር ቅስቀሳ የሚደረገው? ለምንስ ነው በኤርትራ ድንበር ያላቁዋረጠ ትንኮሳ ወያኔ የሚያደርገው?ለምንስ ነው በአገር ውስጥ ራሱ ችግር ፈጥሮ በሻቢያ ወይም በሌሎች የሚያሳበው? ይህን ተራ ፖለቲካ ለምን ያራምዳል? ማንንስ ያታልላል?ኢህአዴግ መንገዳገድ ከጀመረ ከዓመት በላይ ሆኖታል፣ ገደል አፋፍ ላይ ቆሞ ግፉኝ ይላል፣ ባለፈው ዓመት በተባበሩት መንግስታት ግዳጅ ላይ በሱዳን አቢየ ግዛት በፈንጂ ከሃይ በላይ ወታደሮች ሲገደሉ በዉጭ ዜናዎች ሲዘገብ ባገር ዉስጥ ዜናው አልተስራጨም፣በሶማሊያ የኢትዮጵያ ስራዊት ገብቶ ምን ያህል ጉዳት እንደደረስበት ጠያቂም ገላጭም የለም፣በተገባው ቃል መሰረት ባጭር ግዜ (በስድስት ወር) ይወጣል ተብሎ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፣ ማስወጣትም አልተቻለም፣ ቢዝነሱ ቀጥሏል ስራዊቱም ያልቃል ማን ይጩኽለት ጠያቂ ህዝብ/ፓርላማ የለም፣
አጥፍቶ መጥፋትን ግቡ ያደረገው ወያኔ ጠብ ያለሽ በዳቦ እያለ ይገኛል ቶሎ እርምጃ ካልተወስደ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል፣ባለፈው ዓመት በአፋር ክልል በአውሮፓውያን ቱሪስቶች ላይ የተፈፀመው አስቃቂ ግድያ ወንጀሉን ራሱ ወያኔ ለመፈፀሙ ኤዲት ያልተደረገዉ የመጀመሪያዉ የኢቲቬ ዜና ለተመለከተ በቂ ነው፣ከመለስ ዜናዊ አንደበትና ከኢቴቪ ዕለታዊ ዜና የማይጠፉት ሻቢያና ኦነግ ጦርነት አልገጥም አሉ፣ አልሽባብ/አልቃይዳ ኢትዮጵያ የሉም፣ወያኔ ተደራጅቻለሁ እያለ ነው፣ መለስ ዜናዊ የፈራቸው የሙስሊሙ ሶስት ጥያቄዎች በተለያየ ግዜ በፓርላማ አድበስብሶ ከማለፍ ውጪ ቀጥተኛ መልስ አልስጠም፣ ችግሩ እየገፋ መጣ፣ ውሳኔ መስጠት ያልተለማመዱት የወያኔ ባለስልጣኖች እንዴት ዉሳኔ ይስጡ? የራሳቸውን የድርጅት ስራ ማስተካከል ባልቻሉበት ሁኔታ ይህን አደገኛ ጥያቄ በቀላሉ ማተናገድ ከባድ ሆኗል፣ በሃይል ለመጨፍለቅ የማይሞከር ነው፣ከውስጥም ከውጪም የሚያመጣው መዘዝ ስለሚከብድ፣ በመሆኑም ፈራ ተባ እያሉ አንዳንዴም በመኮርኮም ግዜ ማግኘት ብቸኛው አማራጭ ሆኗል፣ ይህ ችግር ሊሰፋና ሌላውን የህብረተስብ ክፍል እየጨመረ ሊሄድ ስለሚችል የመከላከያ ስራዊት ቀን ማዘጋጀትና ወታደራዊ ትርዒት ማሳየት የተሸናፊ መንግስታት ባህሪ በመሆኑ ጭንቅ የወለደው የመከላከያ ቀን/ሳምንት ማለት ይቻላል።  
በሰራዊቱ ዉስጥ መተማመን መጥፋት፣
ባለፈው ወር በቡሬ ግንባር አፋር ክልል ድንበር ጥበቃ ላይ የነበረው ጦር እርስ በርስ መታኮሱን፣ ከአርባ በላይ መኮንኖችና ወታደሮች መሞታቸው፣ከስማኒያ በላይ መቁሰላቸው ተነግሯል፣ በመከላከያም ከዋና መስሪያ ቤት እስከ ድንበር ባሉ የጦር ክፍሎች ድርስ በግምገማ ስበብ በርካታዎች ላይ የተለያየ እርምጃ ተወስዷል፣ ይህም ስራዊቱን እርስ በርስ እንዳይተማመን አድርጎታል፣ ለከፍተኛና  መስመራዊ መኮንኖች የሚስጠው የማዕረግ ዕድገት በስራዊቱ ዉስጥ መነጋገሪያ ሆኗል፣ በተባበሩት መንግስታት ሚሲዮን ግዳጃቸውን ፈጽመው ሲመለሱ የሚከፈላቸው ገንዘብ ትክክል ባለመሆኑ በየግዜው ከግዳጅ መልስ አቤቱታ ይቀርባል ተገቢ መልስ የሚስጥ የለም፣ እንዲያዉም ማስፈራራትና ብሎም ነጥሎ ለማጥፋት ወደ ተለያዩ የጦር ክፍሎች መበታተን ይደረጋል፣ ይህም በተደጋጋሚ ውዝግብ ፈጥሯል፣ደብዛቸው የጠፋ የሰራዊቱ አባላት አሉ፣አብዛኛው የስራዊቱ አባላት በስባት ዓመት አገልግሎት ይስናበታሉ፣በመሆኑም ለስራዊቱ የሚስጡ ጥቅማጥቅሞችን እንደ የቤት መስሪያ ቦታ ኮንዶሚኒየም ቤት አያገኙም፣ ይህና ሌሎችም ችግሮች ተደማምረው ስራዊቱን ክፉኛ ለያይቶታል፣እንኩዋንስ ዘንቦብሽ እንዲያዉም ጤዛ ነሽ እንዲሉ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ በተለያየ መንገድ ስራዊቱን የሚለቁ ቁጥራቸው እየጨመረ ሄዷል ጄኔራል መኮንኖች ጭምር፣
ታዲያ የመከላከያ ስራዊት አዛዥ ማን ነው? እስካሁን አዛዡ መለስ ነበር አሁን የለም፣ ይህ የዕዝ ክፍተት የሚታየው በከፍተኛው ዕርከን ደረጃ በመሆኑ የከፋ ያደርገዋል፣ በቅርቡ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ የስጠውን የአየር ሃይል አዛዥ ከሃላፊነት ማንሳት አለመቻሉ የዚሁ ነፀብራቅ ነው በየትም ዓለም አንድ አዝዥ የስጠው ትዕዛዝ ካልተፈፀመ ወዲያዉኑ ስራዉን ይለቃል። በደርግም ግዜ ተመሳሳይ ችግር ተከስቶ ነበር ጄ/ መርዕድና ጄ/ ገ/ክርስቶስ ቡሊ ወዲያዉኑ ማዕረጋቸዉን ተገፈው ተስናብተዋል፣ አሁን ግን መደበኛ ጦርና አዛዥም ስለሌለ ማን በማን ላይ እርምጃ ይውስድ፣ ይህ አሳዛኝና አሳፍሪ የስነስርዓት ጉድለት ያዉም በከፍተኛ አመራር ደረጃ ይቅርታ የሌለው ነው፣ ስለዚህ ከፍ ብየ እንደጠቀስኩት ሁሉም ሹመትና ቢሮ ተስጣቸው እንጂ ምንም አይነት ስልጣን የላቸውም። ታዲያ በስሞኑ ያከበሩት ቀን ለመተዋወቅና እኔ ነኝ አዛዥህ ለማለት ይሆን ይህስ ተቀባይነት ይኖረዋል?፣ ስራዊቱ በጥቅም፣ በማዕረግ ዕድግት፣በግዳጅ አስጣጥ፣ከፍቶታል፣ከህዝቡ የተፈጠረ በመሆኑ ከራሱ ብሶት ጋር ተዳምሮ ምሬቱን መግለፅ ጀምሯል፣ የህዝቡም ችግር እየከፋ ሄዷል የሙስሊሙን ችግር ደፍሮ ለመፍታት እጁን የሚያስገባ ጠፋ፣ ያለ መለስ የማይንቀሳቀሱ ኢህአዴጋዉያን ሊደማመጡ አይችሉም አሁን ሁሉም የራሱ ጌታ ወደመሆኑ እየሄደ ይመስላል፣የሚስድባቸዉና የሚቆጣቸውም የለም ታዲያ በዚህ ቀውጢ ስዓት ማን አመራር ይስጥ? ህዝብን መፍራት ተጀመረ? ወይስ ሃይል በማሳየት የራስን ህዝብ ማስፈራራት?ተስፋ መቁረጥ በደርግ መውደቂያ ስዓትም ተከስቷል፣ ሹመትና ሽልማት ድግስና ግብዣ አብዝቶ ነበር የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ፣ ስራዊቱን በዚህ ደልሎ መያዝ የዘገየ ነው፣ የተከማቸ ችግር ስላለው ካሁን በሁዋላ በመከላከያ ቀን ምክንያት ህብረትን መመለስ ህዝብንም ማስፈራራት አይቻልም
አስጨናቂ ድረስ  (ከጉለሌ)
baschenaki@gmail.com 

No comments:

Quick Linker

Amazon SearchBox

About the Bloger

My photo

Prof. Muse Tegegne has lectured sociology Change &  Liberation  in Europe, Africa and Americas. He has obtained  Doctorat es Science from the University of Geneva.   A PhD in Developmental Studies & ND in Natural Therapies.  He wrote on the  problematic of  the Horn of  Africa extensively. He Speaks Amharic, Tigergna, Hebrew, English, French. He has a good comprehension of Arabic, Spanish and Italian.